Get Mystery Box with random crypto!

የዐማራን ክልልን መሪ አልባ በማድረግ ያደሩ ጥያቄዎቹን የማዳፈን አደጋ መኖሩን ርእሰ መስተዳድሩ ተ | YeneTube

የዐማራን ክልልን መሪ አልባ በማድረግ ያደሩ ጥያቄዎቹን የማዳፈን አደጋ መኖሩን ርእሰ መስተዳድሩ ተናገሩ!

የዐማራ ክልል ሕዝብ የሚያነሣቸው መሠረታዊ ጥያቄዎች የሚፈቱት፣ በሰላማዊ መንገድ ብቻ ነው፤ ሲሉ፣ የክልሉ ርእሰ መስተዳደር ይልቃል ከፋለ(ዶ/ር) ተናገሩ፡፡ በባሕር ዳር ከተማ፣ ለክልሉ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች የተዘጋጀው እና ትላንት፣ በርእሰ መስተዳድሩ ንግግር በተከፈተው መድረክ፣ ውይይት እየተካሔደ ነው።

ርእሰ መስተዳደሩ፣ በውይይቱ መክፈቻ ንግግራቸው ባስተላለፉት መልዕክት፣ በክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ላይ የሚደረገው የስም ማጥፋት ዘመቻ፣ ክልሉን መሪ አልባ በማድረግ የሕዝቡን ጥያቄ ለማዳፈን የታሰበ ነው፤ ብለዋል።የዐማራ ሕዝብ የአደሩ መሠረታዊ ጥያቄዎች የሚፈቱት፣ ሕዝቡ ከአመራሩ ጋራ አንድነቱን በማጠናከር፣ ከአጎራባች ክልሎች እና ከፌዴራል መንግሥቱ ጋራ በጋራ በመቆም ነው፤ ብለዋል ርእሰ መስተዳድሩ።

የአሜሪካ ድምፅ ያነጋገራቸው፣ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ግን፣ ብልጽግና ፓርቲ ለዐማራ ሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት የሚችለው፣ በውስጡ ያለውን ክፍፍል ቀርፎ፣ እንደ ዋሕድ/አንድ/ ፓርቲ መንቀሳቀስ ሲችል ነው፤ ብለዋል።ትላንት ኀሙስ፣ ግንቦት 10 ቀን 2015 ዓ.ም. የተጀመረውና ለአምስት ቀናት እንደሚቆይ የተነገረው የዐማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች ውይይት፣ በቅርብ ጊዜ፣ በክልሉ ከተከሠቱ ግጭቶች በኋላ የመጀመሪያው ነው።

የውይይቱ ዋና አጀንዳ፣ የአደሩ የዐማራ ሕዝብ ጥያቄዎች መኾናቸውን፣ የክልሉ ርእሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ ተናግረዋል።ርእሰ መስተዳድሩ፣ “ያደሩ” ላሏቸው የዐማራ ሕዝብ ጥያቄዎች፥ የወሰንና የማንነት፣ የሕገ መንግሥት መሻሻል፣ የዜጎች መብት መከበር፣ የጨቋኝ እና ተጨቋኝ ትርክቶች ይስተካከል፤ የሚሉትን ርእሰ ጉዳዮች፣ በማሳያነት ጠቅሰዋል።

እነዚኽ የሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች የሚፈቱትም፣ በሰላማዊ መንገድ ብቻ ነው፤ ብለዋል። ጥያቄዎቹ፣ ቀድሞውኑም የታወቁ ቢኾኑም፣ በተደራጀ አግባብ መልስ እንዲያገኙ እንቅስቃሴ አለመደረጉን የጠቀሱት ርእሰ መስተዳድሩ፣ ያደሩት ጥያቄዎች ከሌሎች ወቅታዊ አጀንዳዎች ጋራ ተደምረው ሕዝቡን ለሌላ ቁጣ እየገፋፉት ናቸው፤ ብለዋል::ይህም ኾኖ፣ ክልሉን በማተራመስ የሚፈታ ነገር እንደሌለና ጥያቄዎቹ ምላሽ የሚያገኙት በኢትዮጵያ ጥላ ሥር እንደኾነ ያስገነዘቡት ርእሰ መስተዳድሩ፣ “የዐማራ ሕዝብ፣ ከአጎራባች ክልሎች እና ከፌዴራል መንግሥቱ ጋራ በመኾን እንዲፈቱ አቋም ይያዛል፤” ብለዋል።

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ትምህርት ክፍል መምህር የኾኑት ረዳት ፕሮፌሰር ኤፍሬም አሐዱ፣ የዐማራ ሕዝብ ያነሣቸው ጥያቄዎች፣ በወቅቱ ምላሽ አለማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ሕዝቡ በተለያየ መንገድ ቁጣውን እየገለጸ ባለበት በዚኽ ሰዓት፣ የዐማራ ብልጽግና ፓርቲ ቁጭ ብሎ መምከሩ ጥሩ ቢኾንም፣ የዐማራ ሕዝብ ጥያቄዎችን ለመፍታት ግን፣ የብልጽግና ፓርቲ አባላት እና አመራሮች፣ እንደ አገር ተናበው እና ተከባብረው በጋራ መሥራት እንዳለባቸው አስረድተዋል።

ረዳት ፕሮፌሰር ኤፍሬም አክለውም፣ ችግሮች ከመፈጠራቸው በፊት፣ የሕዝብን ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት፣ እንዲህ ዐይነት ውይይቶች ቢደረጉ ተገቢ ነበር፤ ብለዋል፡፡የዐማራ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ጽ/ቤት ሓላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ፣ በትላንትናው የውይይት ውሎ ላይ ስለተነሡ ጥያቄዎች፣ በክልሉ መንግሥት ቴሌቪዥን ቀርበው አብራርተዋል፡፡

የገዥው የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና የዐማራ ክልል ጽሕፈት ቤት ሓላፊ የነበሩትን የአቶ ግርማ የሺጥላን ግድያ ተከትሎ፣ በዐማራ ክልል ከፍተኛ የኾነ ጸጥታዊ ውጥረት መፈጠሩን፣ በትላንቱ የመክፈቻ ንግግራቸው የገለጹት ርእሰ መስተዳድሩ ዶ/ር ይልቃል ከፋለ፣ ለወቅታዊ ችግሮች መነሻው ጽንፈኝነት ነው፤ ብለዋል፡፡በባሕር ዳር በተጀመረው በዚኹ ውይይት፣ ከክልሉ ልዩ ልዩ አካባቢዎች የተውጣጡ 1ሺሕ400 የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡

Via VoA
@YeneTube @FikerAssefa