Get Mystery Box with random crypto!

ቤተክህነት  ባቀረበችው የይግባኝ አቤቱታ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለዕሮብ ተቀጠረ! የኢትዮጵያ ኦሮቶዶ | YeneTube

ቤተክህነት  ባቀረበችው የይግባኝ አቤቱታ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለዕሮብ ተቀጠረ!

የኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ተዋህዶ  ቤተክርስቲያን ሀገወጥ ነው በተባለው አዲሱ ሲኖዶስና በሕግ የተጣለባቸውን ግዴታ አልተወጡም በተባሉት የኦሮሚያ ክልል መንግስት፣የፌደራል ፖሊስና የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽኖች ላይ ባቀረበችው የዕግድ አቤቱታ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ፍርድ ቤት ለመጪው ረቡዕ የካቲት 1 ቀን 2015 ዓም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ።

ተለዋጭ ቀጠሮውን የሰጠው አቤቱታው የቀረበለት ልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት መሠረታዊ መብቶች ችሎት ነው። ችሎቱ በዛሬው ዕለት በነበረው ውሎ አቤቱታውን ካቀረቡት የቤተክርስቲያኗ ጠበቆች የተለያዩ የማብራሪያ ጥያቄዎችን በማንሳት ማብራሪያ መጠየቁንና ተገቢው ማብራሪያ እንደተሰጠም ከቤተክርስቲያኗ የችሎት ክርክር ኃላፊነት የተሰጣቸው ጠበቃ አንዷለም በውቀቱ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

ችሎቱ ማብራሪያ ከጠየቀባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ችሎቱ ጉዳዩን የማየት ሰልጣንን አለው የሚለውን እንዲያብራሩ የሚጠይቅ ሲሆን በዚህ ላይም በቂ ማብራሪያ ለችሎቱ መሰጠቱን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ችሎቱ በምን መልኩ ትእዛዝ እንዲሰጥ እንደሚፈልጉ ፣ ትእዛዝ ለማን እንደሚሰጥ ፣ ትእዛዙን ማን እንደሚያስፈጽም እንደሚፈልጉ እንዲሁም የህግ ጥሰት የፈጸመው ማን እንደሆነ እንዲያብራሩ መጠየቃቸውን የጠቆሙት ጠበቃ አንዱአለም ፤ የህግ ጥሰት እየፈጸመ የሚገኘው "ህገ ወጡ ሲኖዶስ" እና የኦሮሚያ ክልል የፀጥታ አካል ስለመሆኑ ማብራራታቸውን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩን ጨምሮ በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት አካላት በተፈጠረው ችግር ላይ የሚሰጡት አስተያየት ችግሩን የሚያወሳስብ በመሆኑ ከዚህ በኋላ በጉዳዩ ላይ ያልተገባ አስተያየት በመስጠት ችግሩን እንዳያባብሱ ትእዛዝ እንዲሰጥ መጠየቃቸውን ገልጸዋል።

[Reporter]
@YeneTube