Get Mystery Box with random crypto!

በሃይማኖት ውዝግብ በሻሸመኔ የተነሳው ሁከት “ሻሸመኔ የተፈጠረው በጣም ሚያሳዝን የሚስለቅስ ነው፡ | YeneTube

በሃይማኖት ውዝግብ በሻሸመኔ የተነሳው ሁከት

“ሻሸመኔ የተፈጠረው በጣም ሚያሳዝን የሚስለቅስ ነው፡፡ ህግ ባለበት አገር ይህ ሁሉ እንደሚመጣ እየተናገርን መንግስት መቆጣጠር ለምን እንደተሳነው ግራ ገባን፡፡ የሚመጣውም ጥሩ አይመስለኝም፡፡”
በዛሬው እለት ኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን ሻሸመኔ ከተማ ከሃይማኖት ጋር ተያይዞ በተነሳው ግጭት የሰው ህይወት ማለፉ ተገለጸ፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የምዕራብ አርሲ፣ ሲዳማ እና ጌዴኦ አገረስብከት ሊቀጳጳስ አቡኔ ዮሴፍ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት በሻሸመኔ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ዛሬ ጠዋት ተከፍቷል ባሉት ጥቃት ከምዕመናን ቢያንስ አንድ ሰው መሞቱ ሲረጋገጥ በርካቶች መጎዳታቸውን አመልክተዋል፡፡

በሌላ በኩል ከሁለት ሳምንት በፊት የኦሮሚያ እና ብሔርብሔረሰቦች ሲኖዶስ በሚል ተሰይመዋል ለተባሉት የሃይማኖት አባቶች በዛሬው እለት በባቱ፣ አሰላ እና ሻሸመኔ አቀባበል መደረጉን ቃል አቀባያቸው ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡

“ሻሸመኔ የተፈጠረው በጣም ሚያሳዝን የሚስለቅስ ነው፡፡ ህግ ባለበት አገር ይህ ሁሉ እንደሚመጣ እየተናገርን መንግስት መቆጣጠር ለምን እንደተሳነው ግራ ገባን፡፡ የሚመጣውም ጥሩ አይመስለኝም፡፡”

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የምዕራብ አርሲ፣ ሲዳማ እና ጌዴኦ አገረስብከት ሊቀጳጳስ አቡኔ ዮሴፍ ዛሬ በሻሸመኔ ከሰሞነኛው የቤተክርስቲያንቱ ውዝግብ ጋር ተያይዞ አለመረጋጋት መፈጠሩን በማስመልከት ለዶይቼ ቬለ የተናገሩት ነው፡፡ በዚህም ዛሬ ጠዋት በከተማዋ ውስጥ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ከምዕመን እና የመንግስት የፀጥታ ሃይሎች መካከል አለመግባባት ተፈጥሮ የሰው ህይወትም ማለፉ ነው የተነገረው፡፡ “አንድ ወጣት ሞቶ ሌላኛውም ቆስሎ ሆስፒታል ገብቷል፡፡ ጉዳተኞቹ እና የሟቾች ቁጥር ግን ከዚህም ከፍ ሊል የሚችልበት እድል አለው፡፡”

በሌላ በኩል በቅርቡ የኦሮሚያ እና ብሔርብሔረሰቦች ሲኖዶስ በሚል ተሰየመ ተብሎ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ተቀባይነቱ ውድቅ በተደረገው ወገን የአደራጅ ኮሚቴ አካል እና ቃል አቀባይ ሆነው የሚያገለግሉት ዲያቆን መርዕድ ቱሉ ለዶቼ ቬለ እንደተናገሩት ግን ተሰይመዋል ላሏቸው አባቶች ሻሸመኔን ጨምሮ በአከባቢው ባሉ ከተሞች አቀባበል ተደርጓል፡፡

እንደ ቃልአቀባዩ ማብራሪያ በሻሸመነ የተፈጠረው አለመረጋጋትና ቶክስም በመንግስት ፀጥታ አካላት ሳይሆን የታጠቁና ቤተክርስቲያን ውስጥ ሆነው ወደ ፀጥታ አካላት በተኮሱ ባሏቸው ነው፡፡ ሻሸመነ አቀባበል ተደረገላቸው ያሏቸው አባቶች ግን ባለው በፀጥታ አለመረጋጋት ወደ ቤተክርስቲያን ዘልቀው አለመግባታቸውን አረጋግጠዋል፡፡

የሃገረስብከቱ ሊቀጳጳስ አክለው እንደተናገሩት ከሆነ ግን አለመረጋጋቱ እስከ አመሻሽ ድረስ ቀጥለዋል፡፡ “ህዝቡ ወንድም እህቶቻችን እያለቁ ነው እያለ ነው፡፡ ቤተክርስቲን ላይ ከፍተኛ ጥቃት ደርሷል፡፡ ህንን የማቆም ሃላፊነት ያለው አካል ሊያስቆመም ይገባል፡፡ በሁሉም አቅጣጫ የጥይት ድምጽ ይሰማል፡፡”

ዛሬ በሻሸመኔ ተፈጥሯል ስለተባለው ከሃይማኖት ጋር ስለተያያዘው አለመረጋጋት ከአከባቢው የፀጥታ ባለስልጣናት ለማረጋገጥ ያደረግነው ጥረት ስልካቸው ባለመነሳቸው አልተሳካም፡፡ ለኦሮሚያ ክልል ፀጥታ አስተዳደር እና ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊዎች እንዲሁም ለፌዴራል መንግስት የኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ደውለንም ተፈጥሯል ስለተባለው ለመጠየቅ ያደረግነው ጥረትም ለዛሬ አልሰመረም፡፡ 

Via:- DW
@Yenetube @Fikerassefa