Get Mystery Box with random crypto!

የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ ሚኒስቴር ከ3 ሺሕ 1 መቶ በላይ ተሽከርካሪዎችን በጊዜያዊነት ከነዳጅ | YeneTube

የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ ሚኒስቴር ከ3 ሺሕ 1 መቶ በላይ ተሽከርካሪዎችን በጊዜያዊነት ከነዳጅ ድጎማው ማገዱን አስታወቀ!

የድጎማ ስርዓቱ ከሚፈቅደው አሠራር ውጭ በሆነ መንገድ የተንቀሳቀሱ ከ3 ሺሕ 1 መቶ በላይ ተሽከርካሪዎች በጊዜያዊነት ከነዳጅ ድጎማው መታገዳቸውን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ ሚኒስቴር አስታወቀ።ሚኒስቴሩ የድጎማ ስርዓቱ ከሚፈቅደው አሠራር ውጭ በሆነ መንገድ ለመጠቀም የተተመነላቸውን የትራንስፖርት ታሪፍ የማያከብሩ፣ የስምሪት መስመራቸውን በአግባቡ የማይሸፍኑ እንዲሁም ከስምሪት ውጪ በመሆን በኮንትራት ሥራ ላይ በመሰማራት ተገቢውን አገልግሎት ለሕብረተሰቡ በማይሰጡ አሽከርካሪዎች ላይ አስተዳደራዊና ሕጋዊ እርምጃ እየተወሰደ እንደሚገኝ ገልጿል።

በዚህም ከሚመለከታቸው ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ተሽከርካሪዎችን ከድጎማ ተጠቃሚነት ምዝገባ እንዲታገዱ በደረሱ ሪፖርቶች መሰረት፤ 3 ሺሕ 1መቶ 40 ተሽከርካሪዎች ከአዲስ አበባ፣ ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ድሬደዋ፣ ጋምቤላ፣ ደቡብ ብ/ብ እና ህዝቦች፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ፌደራል ደረጃ በቀረቡ ሪፖርቶች እንዲታገዱ መደረጉን ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡በድጎማ ስርዓቱ መሰረት የሚጠበቅባቸውን አሟልተው ሲገኙና ተገቢው የሕግ እርምጃ እንደተወሰደባቸው ሲረጋገጥ ዳግም ወደ ድጎማ ተጠቃሚነት እንዲመለሱ በማድረግ አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኝም ተገልጿል፡፡

በክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች የሚካሄዱ የነዳጅ ድጎማ ቁጥጥር ሥራዎችን ለመደገፍ ከብሔራዊ ነዳጅ ድጎማ (NFS) ማስተግበሪያ ስርዓት እና ቴሌ ብር መተግበሪያ ጋር የተሳሰረ የ6006 አጭር መልዕክት ቁጥር  ወደ አገልግሎት ማስገባት መቻሉን የገለጸው ሚኒስቴሩ፤ እስካሁን ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች 2 ሺሕ 2 መቶ የሚደርሱ የቁጥጥር ባለሙያዎችና የትራፊክ ፖሊስ ስልክ ቁጥሮች አገልግሎት እንዲያገኙ መመዝገባቸውን አስታውቋል።

የህዝብ ትራንፖርት ተጠቃሚው ሕብረተሰብ የድጎማ ተጠቃሚ ተሸከርካሪዎች በወጣላቸው ታሪፍ መሰረት  አገልግሎት የማይጡ አካላት ሲያጋጥሙት ጥቆማ የሚያቀርብበት አጭር መልዕክት መቀቢያ ስርዓት ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝም ተነግሯል፡፡

የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በብሔራዊ ድጎማ ማስተግበሪያ ስርዓት ላይ እስከ ጥር 24 ቀን 2015 ድረስ የተመዘገቡ የተሽከርካሪዎች ቁጥር 1 መቶ 95 ሺሕ 73 ሲሆን፤ ከጠቅላላ ተሽከርካሪዎች ውስጥ 1 መቶ 23 ሺሕ1 መቶ 71 የሚሆኑ ተሽከርካሪዎች ነዳጅ በድጎማ  እያገኙ ያሉ ተሽከርካሪዎች ናቸው።መንግስት የነዳጅ ዋጋ ድጎማን በሂደት በማስቀረት ወደ ቀደመው የዋጋ ማረጋጊያ ፈንድ አስተዳደር ሥርዓት ለመመለስ የሚያስችል የዋጋ ማስተካከያ እና የታለመ ነዳጅ ድጎማ ሥርዓት እንዲተገበር በወሰነው መሰረት ከሀምሌ ወር 2014 ጀምሮ የብሔራዊ የታለመለት ነዳጅ ድጎማ ተግባራዊ መደረጉ ይታወሳል፡፡

@YeneTube @FikerAssefa