Get Mystery Box with random crypto!

በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የፍርድ ቤት ውሳኔን የሻረ ሕጋዊ ይዞታን የመንጠቅ ተግባር እየተከናወነ ነው | YeneTube

በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የፍርድ ቤት ውሳኔን የሻረ ሕጋዊ ይዞታን የመንጠቅ ተግባር እየተከናወነ ነው!

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሚ ኩራ ክፍል ከተማ ወረዳ ኹለት አያት መንደር 18 አካባቢ ነዋሪዎች፣ ሕጋዊ ይዞታ የሆነውን የጋራ መናፈሻ፣ የክፍለ ከተማው ባለሥልጣናት ቦታውን በግለሰብ ሥም አዙረው ለመሸጥ የፍርድ ቤት ውሳኔ መጣሳቸው ተገለጸ፡፡እስከ 600 የሚደርሱ አባዎራዎች ሕጋዊ ይዞታ የሆነውና ከ15 ዓመት በላይ የለማውን መናፈሻ፣ የክፍለ ከተማው ባለሥልጣናት ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በትራክተር ማፍረሳቸውን ተከትሎ፣ ባለይዞታዎች ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስደውት ነበር፡፡

በካርታ የተረጋገጠ ሕጋዊ የይዞታ ማረጋገጫ ያላቸው ነዋሪዎቹ፣ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስደው ማሸነፋቸውንም፣ የባለይዞታዎቹ የልማት ኮሚቴ አመራሮች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የልማት ኮሚቴ አመራሮቹ የምጣኔ ሀብት ምሁሩ አለማየሁ ገዳ (ፕ/ር)፣ በላይ ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር)፣ ገበየሁ ተሰማ፣ ይልቃል መለስና ዘውዱ ገብር ማሪያም፤ ከፍርድ ቤቱ ውሳኔ በኋላ ቦታውን መልሶን ለማልማት ከወረዳው ኃላፊዎች ጋር ስምምነት ማድረጋቸውን ጠቁመዋል፡፡ ይሁን እንጂ “ቦታውን ለጊዜው በአጣና ስናጥር፣ በፍርድ ቤት የተረታው ግለሰብ “ድርዬ ሰብስቦ” ዳግመኛ አስፈርሶብናል።“ ሲሉ ባለይዞታዎቹ ገልጸዋል፡፡

አዲስ ማለዳ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ የተመከተች ሲሆን፣ በጉዳዩ ላይ ብይን የሰጠው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የካ ምድብ 5ኛ የፍትሐብሔር ችሎት በ14/07/2014 በዋለው ችሎት፣ ለባለይዞታው ከሳ ወይም ምትክ ሳይሰጥ ከሕግ አግባብ ውጪ በተከሳሽ የተወሰደው ቦታ ለባለይታዎቹ እንዲመለስ ወስኗል፡፡

ባላይዞታዎቹ በፍርድ ቤቱ ውሳኔ መሰረት፣ ቀድሞ የፈረሰውን ቦታቸውን መልሰው ለማልማት ጥረት እያደረጉ ባሉበት በዚህ ወቅት፣ ከክፍለ ከተማ ባለሥልጣናት ጋር ተመሳጥሮ ቦታውን ያስፈረሰው ግለሰብ ዳግም ወጣቶችን ሰብስቦ የቦታውን አጥር ማስፈረሱን የቦታው የልማት ኮሚቴ አባላት ተናግረዋል፡፡

ቀደም ሲል ግለሰቡ ከክፍለ ከተማው ባለሥልጣናት ጋር በመመሳጠር በክፍለ ከተማው ትብብር አፍርሶታል የተባለው የለማ ቦታ፣ በፍርድ ቤት ውሳኔ ከተሰጠበት በኋላ ዳግም ያስፈረሰው፣ ከጀርባው ያሉ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ተገን አድርጎ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

በፍርድ ቤት የተረታው ግለሰብ ሕገ ወጥ ድርጊት፣ ከክፍለ ከተማው ባለሥልጣናት ጋር በመመሳጠር ቦታውን በሥሙ አዙሮ የመሸጥና ከባለሥልጣኖቹ ጋር ለመካፈል ያለመ መሆኑን ባለይዞታዎችነ ባደረጉት ማጣራት መረዳታቸውን ተናግረዋል፡፡ ይህንኑ ብልሹ አሰራር ለማስፈጸም መሬቱ ይገባኛል ብሎ ለቀረበው ግለሰብ፣ ካርታ ባለው ቦታ ላይ ከለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ካርታ ተስርቶ እንደተሰጠው ተስምቷል፡፡

ይሁን እንጂ ቦታው ቀደም ሲል በየካ ክፍለ ከተማ ሥር በነበረበት ወቅት፣ ለነዋሪዎቹ ሕጋዊ የባለቤትነት ማረጋገጫ ካርታ የተሰጠበት መሆኑን አዲስ ማለዳ ነዋሪዎቹ ካቀረቡላት ሰነድ ተመልክታለች፡፡

ይህንኑ የባለቤትነት ካርታ ሕጋዊነት የሚያረጋግጥ የፍርድ ውሳኔ የተሰጠበት ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ውሳኔ ተከሳሹ ነዋሪዎቹ ያለሙትን 10 ሺሕ ሜትር ካሬ የሚገመተውን ቦታ አፍርሶ ማጠሩ ከሕግ አግባብ ውጪ በመሆኑ፣ አጥሩን አፍርሶ ለባለይዞታዎቹ እንዳስረክብ እና የደረሰባቸውን ኪሳራና ወጪ እንዲከፍል ወስኗል፡፡

የቦታው ባለቤቶች ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹ፣ ሕጋዊ የባለቤትነት ካርታ አውጥተው ያለሙት ቦታ የክፍለ ከተማው ባለሥልጣናት በግለሰብ ሥም ቦታውን ቀምተው ለሪል ስቴት አልሚ ለመሸጥ በማሰብ መሆኑ ተነግሯል፡፡ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ በከፍተኛ የሙስና ብልሹ አሰራር በተደጋጋሚ ሥሙ መነሳቱ የሚታወስ ነው፡፡ በዚሁ ችግር ከመሬታ ጋር የተገናኙ አገልግሎቶችን እስከማቋረጥ የደረሰ ችግር አጋጥሞ ነበር፡፡

Via Addis Maleda
@YeneTube @FikerAssefa