Get Mystery Box with random crypto!

83ኛው የአገው ፈረሰኞች ማህበር የምስረታ በዓል ፌስቲቫል በእንጂባራ እየተካሄደ ነው! የአገው | YeneTube

83ኛው የአገው ፈረሰኞች ማህበር የምስረታ በዓል ፌስቲቫል በእንጂባራ እየተካሄደ ነው!

የአገው ፈረሰኞች ማህበር 83ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ፌስቲቫል በእንጂባራ ከተማ በተለያዩ የፈረስ ትርኢቶችና የባህል ቡድኖች ሙዚቃ ታጅቦ በድምቀት እየተከበረ ነው።የአዊ ዞን ብሄረሰብ አስተዳደር የባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ለይኩን ሲሳይ የበዓሉን አከባበር አስመልክተው ለኢዜአ እንደገለፁት በዓሉ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ይከበራል።

የማህበሩ አባላትም የፈረስ ሰላምታ፣ ሽምጥ ግልቢያና የተለያዩ ትርኢቶችን በእንግዶች ፊት በማሳየት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።የብሄረሰቡ ባህላዊ መገለጫ የሆኑ የሙዚቃና ሌሎች ትእይንቶችን በዞኑ ስር የሚገኙ ወረዳዎች ተወካዮች በማቅረብ በዓሉን በማድመቅ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዓሉን በአለም ቅርስነት በማስመዝገብም በአካባቢው ከሚገኙት የዘንገናና ፅርባ ሃይቆች እንዲሁም ፋንግ ፏፏቴ ጋር በማስተሳሰር ዘላቂ የቱሪስት መስህብ ለማድረግ እንደሚሰራም አቶ ለይኩን አስረድተዋል።ይህም ለእንጂባራ ከተማና ለዞኑ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ጉልህ አስተዋፅኦ በሚያበረክት መልኩ እየተሰራ ለመሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል።

የአገው ፈረሰኞች ማህበር ፌስቲቫል “የአገው ፈረስ ባህል” በሚል በኢትዮጵያ ቅርስና ጥበቃ ባለስልጣን በማይዳሰስ ቅርስነት ተመዝግቦ ሰርቲፊኬት ማግኘቱ ተጠቅሷል።የአገው ፈረሰኞች ማህበር ከ62 ሺህ በላይ አባላት ያሉት ሲሆን የምስረታ በዓሉ በየዓመቱ ጥር 23 ቀን በድምቀት የሚከበር ሲሆን፤ የዘንድሮው “አምራች ዘማች” በሚል መሪ ሀሳብ እየተከበረ ነው።

@YeneTube @FikerAssefa