Get Mystery Box with random crypto!

የተሽከርካሪ ነጋዴዎች “አጠራጣሪ ግብይቶች” ሲያጋጥሟቸው፤ ለፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት እንዲያሳ | YeneTube

የተሽከርካሪ ነጋዴዎች “አጠራጣሪ ግብይቶች” ሲያጋጥሟቸው፤ ለፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት እንዲያሳውቁ የሚያስገድድ መመሪያ ተዘጋጀ!

የባለሞተር ተሽከርካሪ ነጋዴዎች የደንበኞቻቸውን ማንነት ለመለየትና ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የአሰራር ስርዓቶችን እንዲያዘጋጁ እና አጠራጣሪ ግብይቶች ሲያጋጥሟቸው ለፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ተቋም ሪፖርት እንዲደርጉ የሚያዝ መመሪያ ተዘጋጀ። በመመሪያው መሰረት፤ የተሽከርካሪ ነጋዴዎች ስለደንበኞቻቸው የሰበሰቧቸውን መረጃዎች ለ10 ዓመታት የማከማቸት ግዴታ ተጥሎባቸዋል።

በፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ተቋም የተዘጋጀው ይህ መመሪያ፤ “በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብን ወይም ንብረትን ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብንና ሽብርተኝነት በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር” በ2008 ዓ.ም. የወጣውን አዋጅ መሰረት አድርጎ ነው። መንግስታዊው ተቋም መመሪያውን ያወጣው፤ “የባለሞተር ተሽከርካሪዎች” ግዢን በመጠቀም በአዋጁ የተጠቀሱ ወንጀሎች እንዳይፈጸሙ ለመከላከል መሆኑን በአገልግሎቱ የሱፐርቪዥን ቡድን መሪ የሆኑት ሙሉጌታ ተመስገን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

መመሪያው “የባለሞተር ተሽከርካሪዎች” በሚል ምድብ ውስጥ የሚያስቀምጣቸው፤ የግል አውቶሞቢል፣ የሕዝብ ማመላለሻ፣ የጭነት ማመላለሻ፣ ጎታች መኪና፣ ባለሞተር ብስክሌት እና ልዩ ተንቀሳቃሽ መሳሪያዎችን ነው። እነዚህ ተሽከርካሪዎች በመካኒካል ወይም በኤሌክትሪክ ኃይል የሚንቀሳቀኑ ሊሆኑ እንደሚችሉ በመመሪያው ሰፍሯል። አዲሱ መመሪያ የሚመለከታቸው “የተሽከርካሪ ነጋዴዎች”፤ የባለሞተር ተሽከርካሪዎችን የሚያመርቱ፣ ከውጭ ሀገራት የሚያስመጡ፣ ወደ ውጭ ሀገራት የሚልኩ፣ የሚያከፋፍሉ፣ የሚቸረችሩ፣ የሚያከራዩ፣ ለሽያጭ የሚደለድሉ እና ከዘርፉ ጋር ግንኙነት ያላቸው ግለሰቦች መሆናቸው በመመሪያው ተቀምጧል። በ2008 ዓ.ም. የወጣው አዋጅ መሰረት፤ የተሽከርካሪ ነጋዴዎች “ፋይናንስ ነክ ያልሆኑ፤ የተሰየሙ የንግድ እና የሙያ ስራዎች” ዘርፍ ውስጥ የሚወድቁ ናቸው።

Via Ethiopia Insider
@YeneTube @FikerAssefa