Get Mystery Box with random crypto!

የአዲስ አበባ ፖሊስ 16 የእጅ ቦንብ፣ 9 ሽጉጥ እና 83 የተለያዩ የሽጉጥ ጥይቶችን ከ11 ተጠርጣ | YeneTube

የአዲስ አበባ ፖሊስ 16 የእጅ ቦንብ፣ 9 ሽጉጥ እና 83 የተለያዩ የሽጉጥ ጥይቶችን ከ11 ተጠርጣሪዎች ጋር በመያዝ ምርመራ እያጣራ እንደሚገኝ አስታወቀ!

በመዲናዋ አዲስ አበባ ከሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ጋር ተያይዞ የተጠረጠሩ በርካታ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር እየዋሉ እንደሚገኙ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡ፖሊስ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች በጦር መሳሪያ ዝውውር በተጠረጠሩ ግለሰቦች መኖሪያ ቤት በተደረገ ብርበራ 9 ሽጉጦች እና በተሽከርካሪ ውስጥ ተደብቆ ሲጓጓዝ የነበረ 16 ቦንብ ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር በመተባበር ከነተጠርጣሪዎቹ ተይዘው ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝ ገልጿል፡፡

በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 እና 14  ከሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ጋር በተያያዘ 4 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተጣራ እነደሚገኝ ያስታውቋል ፖሊስ፤ ሕብረተሰቡ በሰጠው ጥቆማ እና በፖሊስ  ክትትል በተጠቀሱት ወረዳዎች ነዋሪ በሆኑ እና በወንጀሉ በተጠረጠሩ 2 ግለሰቦች መኖሪያ ቤት በተደረገ ብርበራ 5 የተለያዩ ሽጉጦች  እና 53 ልዩ ልዩ የሽጉጥ ጥይቶች መያዛቸውን አስታውቋል፡፡

በተመሳሳይ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 ሚኪሊላንድ ኮንደሚኒየም ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኝ የጋራ መኖሪያ ቤት ውስጥ የአዲስ አበባ ፖሊስ እና የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ባደረጉት ክትትል 4 ሽጉጥ ከ30 መሰል ጥይት እና 1 የእጅ ቦንብ  በብርበራ መያዙ ተገልጿል፡፡ በዚህ ወንጀል የተጠረጠሩ 4 ግለሰቦችም በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንም የአዲስ አበባ ፖሊስ ገልጿል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 በተለምዶ ፊናንስ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የአዲስ አበባ ፖሊስ እና የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ባደረጉት ክትትል የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 5-01928 አ.አ በሆነ ፒካፕ ተሽከርካሪ አካል ውስጥ ተደብቆ ሲጓጓዝ የነበረ 15 የእጅ ቦንብ ከ3 ተጠርጣሪዎች ጋር  በቁጥጥር ሥር ውሏል።

በአጠቃላይ 16 የእጅ ቦንብ፣ 9 ሽጉጥ እና 83 የተለያዩ የሽጉጥ ጥይቶችን ከ11 ተጠርጣሪዎች ጋር ይዞ ምርመራ እያጣራ እንደሚገኝ የገለፀው የአዲስ አበባ ፖሊስ፤ በሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ላይ የሚያደርገውን ክትትል እና ቁጥጥር አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።ሕብረተሰቡም አሁንም አካባቢውን ከፀረ ሰላም ሃይሎች በንቃት እንዲጠብቅ እና ጥቆማና መረጃ በመስጠት ለፀጥታ አካላት እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ፖሊስ ጥሪውን አቅርቧል።

@YeneTube @FikerAssefa