Get Mystery Box with random crypto!

የድንጋዩ ግዝፈት፣ የመቃብሩ ጥልቀትና የመቃብር ዘበኞች የክርስቶስን ትንሳዔ እንዳላስቀሩት ሁሉ | Tadele Tibebu - ታደለ ጥበቡ

የድንጋዩ ግዝፈት፣ የመቃብሩ ጥልቀትና የመቃብር ዘበኞች የክርስቶስን ትንሳዔ እንዳላስቀሩት ሁሉ፤ የዐማራን ትንሣኤ እንደ ዔሳው ብርኩናቸውን የሸጡ የይሁዳ ፍየሎች (The Judas goat) ሆኑ፣ የሀገሪቱ ፊልድ ማርሻሎች አያስቀሩትም። እስራኤላውያን ከፈርዖን ባርነት ነፃ ለመውጣት የፈጀውን ያህል ግዜ ይወስድ እንደሆነ እንጂ
እንደ ኡጋንዳው ኢዲ አሚን ዳዳ ያሉ አምባገነኖች የዐማራ ትንሣኤን አያስቀሩትም። እንደ ፕሮፌሰር አሥራት ያሉ ተቆርቋሪ ዐማሮችን ልክ እንደ "ቀያፋ" እንዲያዙ ምክር የሚሰጡ ተላላኪዎች ትንሳኤውን አያስቀሩትም። በኢየሩሳሌም ሊቀ ካህናት የነበረው ቀያፋ እየሱስን ለማስያዝና ፍርድ እንዲፈረድበት፣ "ሕዝብ ሁሉ ከሚጠፋ አንድ ሰው ቢሞት ይሻላል" ብሎ የመከረ ሰው ነው። ምክሩ ግን የክርስቶስን ትንሳኤ አላስቀረውም።

በአንጻሩ፣ ዛሬ ትንሳኤ ላይ ያሉ የሚመስላቸው መጨረሻቸው እንደ አሚን ዳዳ ስደተኛና ፍርደኛ እንደሚሆኑ ምንም ጥርጥር የለም። "ያለምንም ደም፤ ያለምንም ደም" (With out blood, without blood) በሚል መፎክር የተጀመረው የደርግ አብዮት ኢትዮጵያውያንን በመረፍረፍ ከተጠናቀቀ በኋላ፣ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም የሞት ጠረን ሸተተኝ ብሎ ፈርጥጦ ዝምባዋብዌ ገብቷል። የደርግን ሥርዓት በቀይ ሽብር በመደዳ ጭፍጨፋ ገድሎ የሸጠው ሬሳ የብረት ዓምድ ሆኖ አላስቆመውም። የዘረፈው ንብረት መሰላል ሆኖ አላቆየውም። ይልቁንስ እንደ በግ እየነዳ ያረደው የደም ጎርፍ ጠራርጎ ወሰደው። በነ ማርክስ ቴዎሪ የረገጠው ሃይማኖት እንጦሮጦስ አወረደው።

ዛሬ ትንሣኤ ላይ ያሉ የሚመስላቸው አምባገነኖች
የዐማራን ህዝብ እንደ ሂትለር፣ ሙሶሎኒ፣ ስታሊን፣ ፓል ፖት እያሰቃዩ፣ እየጨፈጨፉና እያፈናቀሉ መሠረትነው የሚሉት ርዕዮተዓለም እንደ ናዚ ፓርቲ መንኮታኮቱ አይቀርም። ወለጋ ውስጥ አንዲት የ6 ዓመት ህፃን "ወላሂ ሁለተኛ ዐማራ አልሆነም" እያለች በጉንጮቿ ያፈሰሰችው ዕንባ፣ እየተሳለቁ!..ለማየት በሚያሣሣ ገላዋ ላይ እሽቅድምድም በሚመስል መልኩ ባዘነቡት የጥይት አረር ያፈሰሱት ደሟ የእንጦሮጦስን ጎዳና መጥረጉ አይቀርም።

ይህ ታሪክ ከሩዋንዳዋ ህፃን ጋር የሚመሳሰል ነው። ሩዋንዳ ውስጥ በነበረው ፍጅት ወቅት አንዲት የ7 ዓመት ህፃን በሁቱ ገዳዮች ተከባ "እባካችሁ አትግደሉኝ። ከእንግዲህ ቱትሲ አልሆነም" (Please don't kill me, I will never be a Tutsi again) እያለች መማፀኗን ተከትሎ የዓለምን ልብ ሰብረው ነበር። ይህ የሁቱዎች ጭካኔ የተቱሲዎችን ትንሣኤ አላስቀረውም። ቱትሲዎች ሥልጣን ይዘው በደም የታጠበችውን ሩዋንዳን ውብና ፅዱ፣ የቱሪስቶች መዳረሻ፣ ለኢንቨስትመንት ተመራጭ አደረጓት። ከትንሣኤው በኋላ የሩዋንዳ ህፃናቶች በውቧ ኪጋሊ ከተማ መናፈሻዎች ሲቦርቁ ታዩ።

ዛሬም በአዳነች አበቤ የከንቲባነት ዘመን በአዲስአበባ ከተማ ቤታቸው ፈርሶ መጠጊያ አጥተው የሚንከራተቱ፣ በፈረስ ጋሪ ከቤት እቃ ጋር ተጭነው የሚሰደዱ ህፃናቶች ዕንባ በዮዲት ጉዲት የወረደውን አይነት መቅሰፍት ማምጣቱ አይቀርም። ግፈኞች ወደ ከርሠ መቃብርና ወህኒ ሲወርዱ፣ የአዲስአበባ ህፃናቶች፣ የወለጋ ህፃናቶች፣ ተፈናቀለው በመጠለያ ካምፕ የሚገኙ ህፃናቶች የሩዋንዳን አይነት የትንሣኤ ዘመን ይመጣላቸዋል።

የግፈኞች መጨረሻ ግን እንደ መንጌ መፈርጠጥ፤ እንደ ዣን ፖል እስርቤት መሆኑ አይቀርም። የሩዋንዳዋ ታባ ከተማ ከንቲባ የነበረው "ዣን ፖል አካይሱ" በፈፀመው የዘር ጭፍጨፋና ሰብዓዊ መብት ጥሰት ከፍርድ እንዳላመለጠው ሁሉ፣ አዲስአበባ ላይ እንደ ዣን ፖል ግፍ እየፈጸሙ ያሉ ሰዎች ዕጣ ፈንታ እንደ ዣን ፖል ይሆናል። በወቅቱ ባንኩና ታንኩ በእጃችን ነው ብለው በጥጋባቸው ቦሲኒያን የጨፈጨፉት ጄነራል ራዲስላቭ ክርስቲች እና ኮማንደር ራትኮ ምላዲች ከፍርድ አላመለጡም። ስለዚህ ግፈኞች ሲዋረዱ እንጂ ትንሳኤን አስቀርተው አያውቁም። ናዚዎች በኑምበርግ ፍርድቤት ቀርበው የዕድሜ ልክና የስቅላት ቅጣታቸውን አገኙ እንጂ፣ የእስራኤላውያንን ትንሳኤ አላስቀሩትም። ሁቱዎች በወረንጦ እየተለቀሙ ፍርዳቸውን አገኙ እንጂ የቱትሲዎችን ትንሣኤ አላስቀሩትም። ኢትዮጵያ ላይ ይህ ዘመን አይርቅም።

ከስቅለት በኋሏ ትንሳኤ፤ ከጨለማ በኋላም ብርሀን አለና!