Get Mystery Box with random crypto!

3 ዜናዎች 1፤ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ምክር ቤት በጋዜጠኞች ላይ የሚመሠረቱ ክሶች 'በመገና | Muktarovich Ousmanova

3 ዜናዎች

1፤ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ምክር ቤት በጋዜጠኞች ላይ የሚመሠረቱ ክሶች "በመገናኛ ብዙኀን አዋጅ ብቻ" እንዲታዩ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ጠይቋል። ምክር ቤቱ በታሠሩ ጋዜጠኞች ላይ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እየተፈቀደባቸው መታሠራቸው "ተቀባይነት የሌለው ነው" በማለት ድርጊቱን አውግዟል። ጋዜጠኞች በመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች "ከሕግ አግባብ ውጭ መያዛቸው፣ መታፈናቸውን" የጠቀሰው ምክር ቤቱ፣ የመገናኛ ብዙኀን ተቋማት "ያለ ፍርድ ቤት ማዘዣ ብርበራ" እንደሚፈጸምባቸው አመልክቷል።

2፤ የኢትዮጵያ መንግሥት በሳዑዲ ዓረቢያ በቤት ሠራተኛነት ቀጥረው የሚሠሩ ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 40 የሚኾኑ 500 ሺህ ሠራተኞችን እየመለመለ መኾኑን አልጀዚራ ዘግቧል። አማራ ክልል ብቻ 150 ሺህ አመልካቾችን እንዲመዘግብ በመንግሥት መታዘዙን መናገሩን ዘገባው አመልክቷል። ተቀጣሪ ሠራተኞች ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ በመንግሥት ወጪ እንደሚጓዙና ወርሃዊ ደመወዛቸው 1 ሺህ የሳዑዲ ሪያል ወይም 266 የአሜሪካ ዶላር እንደሚኾን ዘገባው አመልክቷል። መንግሥት አመልካቾች እንዲመዘገቡ በተለያዩ ከተሞች ጥሪ ሲያደርግ ሰንብቷል ተብሏል።

3፤ በሱዳን ጦር ሠራዊትና በፈጥኖ ደራሹ ሠራዊት መካከል ከቅዳሜ ጀምሮ በቀጠለው ግጭት በትንሹ 97 ሰላማዊ ሰዎችና 45 ወታደሮች መገደላቸውንና ከ940 በላይ ሰዎች መቁሰላቸውን የሱዳን ሐኪሞች ቡድን ማስታወቁን ሮይተርስ ዘግቧል። ዛሬ ካርቱም ውስጥ በጦር ሠራዊቱ ዋና ወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያ አካባቢ ውጊያ ሲካሄድ መዋሉን የጠቀሰው ዘገባው፣ የሱዳን ጦር ሠራዊት ብሄራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያውን መልሶ መቆጣጠሩ አመልክቷል። የፈጥኖ ደራሹ ሠራዊት ዋና አዛዥ ጀኔራል ሞሐመድ ሐሚቲ፣ ዓለማቀፉ ኅብረተሰብ "እስላማዊ አክራሪ" እና "ወንጀለኛ" ባሏቸው በባላንጣቸው የጦር ሠራዊቱ ዋና አዛዥ ጀኔራል ቡርሃን ላይ ርምጃ እንዲወስድ በትዊተር መልዕክታቸው ጠይቀዋል።
via ዋዜማ