Get Mystery Box with random crypto!

ለግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በአዲስ መልክ ፍቃድ ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ | Muktarovich Ousmanova

ለግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በአዲስ መልክ ፍቃድ ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን ገለጸ።


የፌዴራል የትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በአዲስ መልክ ፈቃድ ለመሥጠት የሚያስችለውን ምዝገባ እያካሄደ ይገኛል።

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ሽፈራው ሽጉጤ ለኢዜአ እንደገለጹት ተቋማቱን በአዲስ መልክ መመዝገብና ዕድሳት መስጠት በዘርፉ የሚታየውን ሕገ-ወጥ አሰራር ለመከላከል ያስችላል ብለዋል።

ተቋማቱ ከሚነሱባቸው ሕገ-ወጥ ተግባራት መካከል ፍቃድ ባልተሰጠባቸው የትምህርት መስኮችና ካምፓሶች ማስተማርን ጨምሮ ከተፈቀደላቸው በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ የማስተማርና ሐሰተኛ ማስረጃ የመስጠት ተግባር ይገኝበታል።

በአሁኑ ወቅት በዘርፉ ያሉት መመሪያዎችን የማሻሻል ሥራ መጠናቀቁን ያመለከቱት ዋና ዳይሬክተሩ ወደ ሥራ ከመገባቱ በፊት ከግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር ውይይት እንደሚደረግ ገልጸዋል።

ውይይቱ በትምህርት ጥራት ላይ ክፍተት እንዲፈጠር ምክንያት የሆኑ አሰራሮችን በተደራጀ መንገድ ለመቀነስና በሂደትም ለማስወገድ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል።

በዘርፉ የተሻሻለው መመሪያ በግል የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

ባለሥልጣኑ ከሕዳር 30 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ አዲስ ለሚከፈቱ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፈቃድ መሥጠት ማቆሙንም ተናግረዋል።

ምዝገባውን በዘንድሮ ዓመት በማጠናቀቀም በመጪው የ2016 ዓ.ም አዲስ ፍቃድና የእድሳት አገልግሎት መስጠት ሊጀመር እንደሚችል ነው የገለጹት።

በመሥራት ላይ ያሉ ሁሉም የግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሙሉ በተቀመጠው የመመዘኛ መስፈርት መሰረት እንደ አዲስ ምዝገባ መፈጸም እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል።

(ኢፕድ)