Get Mystery Box with random crypto!

††† እንኳን ለተፍጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ዼጥሮስ እና ለ150ው ቅዱሳን ሊቃውንት ዓመታዊ በዓል በሰላ | ✞ገድለ ቅዱሳን✞

††† እንኳን ለተፍጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ዼጥሮስ እና ለ150ው ቅዱሳን ሊቃውንት ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ ዼጥሮስ ሰማዕት †††

††† የቅዱሳን ሰማዕታት መነሻቸው ቅዱስ እስጢፋኖስ ሲሆን ፍጻሜአቸው ደግሞ ቅዱስ ዼጥሮስ ሊቀ ዻዻሳት ነው::

ይህ ቅዱስ የሚታወቀው "ተፍጻሜተ ሰማዕት (የሰማዕታት መጨረሻ)" በሚለው ስሙ ነው:: ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-
የቅዱሱ ሃገረ ሙላዱ ግብጽ ናት:: ዘመኑም 3ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው:: ወላጆቹ ካህን ቴዎድሮስና ቡርክት ሶፍያ ልጅ አጥተው ሐምሌ 5 ቀን ወደ ፈጣሪ ቢማጸኑ በራዕይ ዼጥሮስ ወዻውሎስ ተገልጠው ብሥራትን ለሶፍያ ነገሯት:: በወለደችው ጊዜም በራዕዩ መሠረት "ዼጥሮስ" አለችው::

ሰባት ዓመት በሆነው ጊዜም ለቤተ እግዚአብሔር ሰጥተው በሊቀ ዻዻሳቱ ቅዱስ ቴዎናስ እጅ አደገና በወጣትነቱ ሊቅ: ጥዑመ ቃልና በጐ ሰው ሆነ:: ዲቁናና ቅስናን ተሹሞ ሲያገለግል ቅዱስ ቴዎናስ በማረፉ ቅዱስ ዼጥሮስን የግብጽ 17ኛ ፓትርያርክ አድርገው ሾሙት::

ዘመኑ ደግሞ እጅግ ጭንቅ ነበር:: ክርስቲያኖች በተገኙበት ስለሚገደሉ: አብያተ ክርስቲያናትም ስለ ተቃጠሉ የቅዱሱ መከራ የበዛ ነበር:: ለ14 ዓመታት በፍጹም ትጋት ከመንጋው ጋር ተጨነቀ::

አርዮስን (ተማሪው ነበር) አውግዞ ለየው:: ከጌታ ጋርም ብዙ ጊዜ ተነጋገረ:: ብዙ ተአምራትንም ሠራ:: በዚህ ሁሉ ጊዜ አንድም ቀን በመንበረ ዽዽስናው ላይ አልተቀመጠም:: በሁዋላ ግን ጨካኙ ንጉሥ እንዲገደል አዘዘ::

ሕዝቡ "ከእሱ በፊት እኛን ግደሉን" በማለታቸው ሁከት እንዳይነሳ ቅዱስ ዼጥሮስ ተደብቆ ሔደና በፈቃዱ ለወታደሮች ተሰጠ:: በዚያች ሌሊትም የእርሱ ደም የግፍ ማብቂያ እንዲሆን እያለቀሰ ጮኸ:: ከሰማይም "አሜን! ይሁን!" የሚል ቃል መጣ:: ያን ጊዜ የእርሱ አንገት ተሰየፈ:: ዘመነ ሰማዕታትም አለፈ::

††† የቅዱሳንን ዝክር ከማንበብ ባለፈ በስማቸው መጸለይ (ዘፀ. 32:13): በምጽዋትም ማሰብ (ማቴ. 10:41) ይገባል::

††† ወርኀ የካቲትን ይባርክልን!

††† የካቲት 1 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1."150"ቅዱሳን ሊቃውንት ዻዻሳት (በቁስጥንጥንያ ተሠብሥበው መናፍቃንን ያወገዙበት: ትምሕርተ ቤተ ክርስቲያንን ያፀኑበት /ጉባዔ ቁስጥንጥንያ/ በ381 ዓ/ም::
ከወቅቱ ቅዱሳን ሊቃውንት እነዚህ ይጠቀሳሉ:-
*ቅዱስ ጐርጐርዮስ ዘኑሲስ
*ቅዱስ ጐርጐርዮስ ዘእንዚናዙ
*ቅዱስ ጢሞቴዎስ ዘአልቦ ጥሪት
*ቅዱስ ቄርሎስ ዘኢየሩሳሌም)
2.ቅዱስ ዼጥሮስ ተፍጻሜተ ሰማዕት (ቅዳሴ ቤቱ)
3.ታላቁ ቴዎዶስዮስ ጻድቅ (ንጉሠ ቁስጥንጥንያ)

††† ወርሐዊ በዓላት
1.ልደታ ለቅድስት ድንግል ማርያም እግዝእትነ
2.ቅዱስ በርተሎሜዎስ ሐዋርያ
3.ቅዱስ ሚልኪ ቁልዝማዊ
4.ቅዱስ ራጉኤል ሊቀ መላዕክት
5.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና

††† "ስለዚህ በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያንን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ዻዻሳት አድርጎ ለሾመባት: ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ:: ከሄድሁ በሁዋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ እኔ አውቃለሁ:: ስለዚህ 3 ዓመት ሌሊትና ቀን በእንባ እያንዳንዳችሁን ከመገሰጽ እንዳላቁዋረጥሁ እያሰባችሁ ትጉ::" †††
(ሐዋ. 20:28)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††