Get Mystery Box with random crypto!

ʺ ኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ከፍተኛ ተጋድሎ እያደረጉ ነው' የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዲ | Amhara Police Commission

ʺ ኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ከፍተኛ ተጋድሎ እያደረጉ ነው" የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዲያቆን ተስፋው ባታብል

ዋና አስተዳዳሪው ሁሉም ከዳር ዳር በመነሳት እንዲታገል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የሕወሃት የሽብር ቡድን በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ዳግም ወረራ ከከፈተ ቀናት ተቆጥረዋል፡፡

ሕዝብን ጠላት አድርጎ የተነሳው የሽብር ቡድኑ ወረራ በከፈተባቸው አካባቢዎች በደሎችን እየፈጸመ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆችም የጠላትን ሕልም ለማምከንና ሀገራቸውን ለማጽናት እየተዋደቁ ነው፡፡

የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አስታዳደሪ ዲያቆን ተስፋው ባታብል የሕወሃት የሽብር ቡድኑ ለሰላም የቀረበለትን አማራጭ ወደጎን በመተው ዳግም ጦርነት መክፈቱን ገልጸዋል፡፡

ጦርነቱን ጀምሮ መንግሥትን መክሰሱንም ተናግረዋል፡፡ ጠላት ከጦርነት ውጭ ሌላ ሥራ እንደሌለው ጠንቅቀን እናውቃለን ያሉት ዋና አስተዳደሪው፤ ዋነኛ ጠላታችን እንደሆነ በማንሳት መመከት የሚያስችል ውይይትና ዝግጅት ስናደርግ ቆይተናልም ብለዋል፡፡

የሽብር ቡድኑ የከፈተውን ዳግመኛ ወረራ ለመመከት የመከላከያ ሠራዊት አስደናቂ ተጋድሎ ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡

የመከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻውና ፋኖው ጠላትን እያረገፈው እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

ሕዝቡ ለጀግናውን ተዋጊ ኃይል እውነተኛ ደጀን እንዲሆን እየሠሩ መሆናቸውንም አስታውቀዋል፡፡

ማኅበረሰቡ እያደረገው ያለው አስተዋጽዖ የሚደነቅ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ የፈለገው ቢሆን ጠላት ሊያሸንፈን አይችልም፣ ጠላት የትም አይደርስም፣ ይህን የሚያደርግ ሥራ እየሠራን ነው ብለዋል፡፡

ጦርነቱ ባለበት አካባቢ ያለው ማኅበረሰብ በእልህና በወኔ ተነስቶ ጠላትን እየተፋለመ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የዞኑ የሥራ ኃላፊዎች ከጸጥታ ኃይሉ ጋር በቅንጅት እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የራያ ጀግኖች አካባቢያችንን አንለቅም ብለው ከጠላት ጋር እየተዋደቁ መሆናቸውንም አንስተዋል፡፡

አብዛኛው ማኅበረሰብ ከአሁን ቀደም ከነበረው ወረራ ትምህርት በመውሰድ ከጠላት ፕሮፓጋንዳና የሐሰተኛ መረጃዎች ራሱን እየጠበቀ እንደሆነ የተናገሩት ዋና አስተዳደሪው።

ጠላት ደረሰብን እንጂ አልደረስንበትም፣ የትኛውም ማኅበረሰብ አካባቢውን ለቅቆ የትም መሄድ የለበትም፣ በጀግንነት መታገል አለበት፣ ታግሎ ማሸነፍ አማራጭ የሌለው ምርጫ ነውም ብለዋል፡፡

ሁሉም ከዳር ዳር በመነሳት መታገል እንደሚገባውም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ጀግኖቻችን በማጀገንና ከአሉባልታ በመቆጠብ ጠላትን መምታት ይገባልም ብለዋል፡፡

ለሕዝብ መድረስ ያለበትን መረጃ እናደርሳለን ያሉት ዲያቆን ተስፋው፤ ከዚያ ውጭ ባሉ ጠላት በሚያሰራጫቸው አሉባልታዎች መደናገር እንደማይገባም ገልጸዋል፡፡ ጠላት በተቀላቢ የማኅበራዊ ሚዲያ አርበኞቹ የተሳሳተ የጦርነት ዘገባና ሌሎች አሉባልታዎችን እንደሚያስተላልፍ መታወቅ አለበትም ብለዋል፡፡

በማኅበራዊ ሚደያ አሉባልታዎችን የሚያስተላልፉ ግለሰቦች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም አሳስበዋል፡፡ ማኅበረሰቡ ከበሬ ወለደ ወሬ ራሱን እንዲጠብቅም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ጦርነት ወደ ፊትም፣ ወደ ኋላም ሊል ይችላል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው፤ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ከፍተኛ ተጋድሎ እያደረጉ ነው፣ ከማኅበረሰቡ የሚጠበቀው ተዋጊውን ኃይል ማጀገን ነው፣ የፈለገ ቢሆን ጠላት የትም ሊደርስ አይችልም ነው ያሉት፡፡

ማኅበረሰቡ ከደጀንነት ባለፈ ተዋጊ ኾኖ ጠላቱን መቅጣት አለበት ብለዋል፡፡ ያለ መስዋዕትነት ድል እንደማይመጣም ገልጸዋል፡፡

በአሸናፊነት ስነ ልቦና የተገነባ ማኅበረሰብ ማሸነፉ አይቀርምም ብለዋል፡፡ ከዚሕ በኋላ ከጠላት ጋር መለሳለስ እንደማይገባም ገልጸዋል፡፡

ለጠላት ግብዓት የሚያቀብሉ ባንዳዎች እንዳሉ ያነሱት ዋና አስተዳደሪው እውነተኛ አማራ፣ እውነተኛ ኢትዮጵያዊ ሆነን ምንም ነገር ለጠላት እንዳይደርሰው በማድረግ መቅጣት ይገባል ነው ያሉት፡፡

የሽብር ቡድኑ የመጨረሻ ጠላታችን ነው፣ በአንድ ልብ ቆመን፣ ሃብትና ጥቅማጥቅም ሳይደልለን ጠላትን መዋጋት መቻል አለብንም ብለዋል፡፡

ዘገባው የአሚኮ ነው