Get Mystery Box with random crypto!

አሸባሪው ህወሓት ቡድን ወደ ትግራይ ክልል ሊያስገባ የነበረው አደገኛ ዕፅ ተያዘ ** አሸባሪው | Amhara Police Commission

አሸባሪው ህወሓት ቡድን ወደ ትግራይ ክልል ሊያስገባ የነበረው አደገኛ ዕፅ ተያዘ
**

አሸባሪው የህወሓት ቡድን ከአዲስ አበባ እስከ ሚሌ ኔትወርክ በመዘርጋት በአፋር ክልል በኩል ወደ ትግራይ ክልል ሊያስገባው የነበረ በርካታ ኩንታል አደገኛ ዕፅ በህብረተሰቡ ጥቆማ እና በፖሊስ ብርቱ ክትትል ነሐሴ 19 ቀን 2014 ዓ.ም መያዙን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስታወቀ።

ሁለት ተጠርጣሪዎች በሰሌዳ ቁጥር አ.አ ኮድ 3-A40101AA ቶዮታ ዶልፊን ተሽከርካሪ ላይ አደገኛ ዕፁን ጭነው ሲያጓጉዙ በህብረተሰቡ በተሰጠው ጥቆማ መሰረት ከሌሎች የፀጥታ እና ደህንነት አካላት ጋር በመቀናጀት በቁጥጥር ስር ማዋሉን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጠቅሷል።

ከአደገኛ ዕፁ በተጨማሪ ለእኩይ ዓላማ ማስፈፀሚያ ሊውል የነበረ ሁለት ሚሊዮን ሦስት መቶ ሰባ ሺህ ብር (2,370,000.00 ብር) መያዙንም ገልጿል።

በህወሓት የሽብር ቡድን አባልነት ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት ሁለቱ ተጠርጣሪዎች በሚጠየቁበት ጊዜ አደገኛ ዕፁን የእርዳታ እህል የጫኑ ተሽከርካሪዎችን በመጠቀም ወደ ትግራይ ክልል ለማስገባት እንደሆነ ተናግረው ዕፁን ለመቀበል የተዘጋጀ ቡድን እንዳለም ጠቁመዋል።

ፖሊስም ይህንን ቡድን በቁጥጥር ስር ለማዋል በክትትል ላይ መሆኑን አስታውቋል።

ይህ የሽብር ቡድን ዕፁን ሊያስተላልፍ የነበረው እንደለመደው የትግራይ ወጣቶችን በዕፅ አደንዝዞ ወደ ጦርነት ለመማገድ እንደነበረ በቁጥጥር ስር የዋሉት ተጠርጣሪዎቹ ተናግረዋል።

ይህ አደገኛ ዕፅ የተያዘው በህዝቡ ጥቆማና ቀና ትብብር በመሆኑ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ላቅ ያለ ምስጋናውን እያቀረበ በየትኛውም ደረጃ የሚወጠኑ መሰል የወንጀል ተግባራትን ለመቆጣጠር ህብረተሰቡ ከፀጥታ አካላት ጋር ተገቢውን ቅንጅት በማድረግ የዜግነት ድርሻውን እንዲወጣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጥሪውን አቅርቧል።

EBC