Get Mystery Box with random crypto!

የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት በሚያውክ አካል ላይ አስፈላጊው እርምጃ  እንደተወሰደ  በምዕራብ ጎጃም | Amhara Police Commission

የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት በሚያውክ አካል ላይ አስፈላጊው እርምጃ  እንደተወሰደ  በምዕራብ ጎጃም ዞን የፍኖተ-ሠላም ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዋና ኢንስፔክተር ደሳለኝ ቀሬ ተናገሩ።

ዋና ኢንስፔክተር ደሳለኝ ቀሬ ከአማራ ክልል ፖሊስ ሚዲያ ጋር በነበራቸው ቃለ-ምልልስ እንደገለጹት በክልላችን የትህነግ የሽብር ቡድን በከፈተብን ወረራ የከተማው የፀጥታ ኀይልና ወጣቱ ከፌደራል እና ከክልል የፀጥታ ኀይል ጎን በመሆን ትልቅ ተጋድሎ ማድረጉን ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ ከህልውና ዘመቻው ማግስት ህገ-ወጥነት ተንሰራፍቶ የቆየ ሲሆን በተለይ ህገ-ወጥ የጥይት ተኩስ ከፍተኛ ስጋትን ፈጥሮ እንደነበር የተናገሩት ዋና ኢንስፔክተር ደሳለኝ ቀሬ ከህዝብ ጋር በተደረገ ውይይት እና በተወሰደ ህግን የማስከበር ሂደት አሁን ላይ አንጻራዊ ሰላም ሰፍኗል ብለዋል።

የፍኖተ ሠላምን ከተማ ፀጥታ ለማስቀጠል ከሃይማኖት አባቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች እና ከልዩ ልዩ የጸጥታ አደረጃጀቶች ጋር በመቀናጀት ሰላምና ደኅንነት እንዲረጋገጥ እየሠሩ መኾናቸውንም ዋና ኢንስፔክተር ደሳለኝ አስታውቀዋል።

የሚፈጠሩ የወንጀል ድርጊቶችን በዘላቂነት ለመፍታት የፀጥታ ኀይሉ ቀን ከሌት በመስራት ላይ መኾናቸውን የገለጹት ኀላፊው፤ ወጣቶቹ ከከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ በሚሰጣቸው ትዕዛዝ መሰረት ከፀጥታ ኀይሉ ጎን በመቆም ግዳጅ እና ተልዕኳቸውን በመወጣት አመርቂ የፀጥታ ስራ እየሰሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።

የህግ የበላይነትን ከማረጋገጥ አንፃር ወንጀለኞችን እና የወንጀል ተጠርጣሪዎችን ለህግ አሳልፎ በመስጠት እራሳቸውን ከጸጥታ ኀይሉ ጋር አቀናጅተን እየሰራን ነው ያሉት ደግሞ ፲ አለቃ ጨመረ አጥናፍ ናቸው።

በከተማዋ ሁለተኛ ጣቢያ መከፈቱ አበረታች ተግባር መሆኑን የገለፁት ፲ አለቃ ጨመረ አጥናፍ የከተማውን ፀጥታ ለማስቀጠል በትጋት እንሰራለን ሲሉ ለአማራ ክልል ፖሊስ ሚዲያ ዋና ክፍል ገልጸዋል።

አሁን ላይ አልፎ አልፎ የሚከሰቱ የወንጀል ድርጊቶችን ለማስቆም አጥፊዎችን በማጣራት እና መረጃዎችን በመሰብሰብ የተደራጀ እና የተጠናከረ የስምሪት አቅጣጫ በማስቀመጥ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስዱ የፍኖተ-ሠላም ከተማ ፖሊስ አስታውቋል።

ከስር ያለውን ሊንክ በመጫን የቴሌግራም ቻናላችንን ይመልከቱ!!
https://t.me/joinchat/AAAAAFic4YUKzCmrKYI8YA
የዩቲዩብ ቻናላችንን ሊንኩን በመጫን
https://yt6.pics.ee/3z7l7q