Get Mystery Box with random crypto!

'የሀገር ግንባታ ላይ ሚዲያ ጉልህ ሚና አለው' የአራዳ ክፍለ ከተማ ኮሙኒኬሽን | የጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ እውነተኛ ደጋፊዎች

"የሀገር ግንባታ ላይ ሚዲያ ጉልህ ሚና አለው"

የአራዳ ክፍለ ከተማ ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት በክፍለ ከተማው ከሚገኘው የኦሮሚያ ወጣት ማህበር ጋር በማህበራዊ ሚዲያ እና በሌሎች የኮሙኒኬሽን አግባቦች መረጃዎችን ለህብረተሰቡ ማድረስ በሚቻልበት ሁኔታ ዙሪያ መወያየታቸውን አስታወቀ፡፡

የአራዳ ክፍለ ከተማ ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ በላይነህ ሙሉጌታ የተግባቦት ደረጃን ከፍ ለማድረግ ለኦሮመኛ ቋንቋ ተናጋሪ የማህበሩ አባላት በማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምና በኮሙኒኬሽን ስራዎች ዙሪያ ግንዛቤ ወስደው ወደስራ እንዲገቡ ስልጠና መስጠቱ አስፈላጊ ነው ብለው በቀጣይም ከአምስት በላይ በሚሆኑ የሀገራችን ቋንቋዎች መረጃዎችን በማድረስ ህብረ ብሔራዊ በሆነ መልኩ እንሰራለን ብለዋል፡፡

በአብዛኛው የክፍለ ከተማችን ወጣቶች ጥያቄ መሰረት በኦሮምኛ ቋንቋ የሚዲያ አማራጭ የከፈትን ሲሆን ሚዲያ አጠቃቀም ላይ በጋራ ልንሰራ ይገባል ያሉት አቶ በላይነህ ትክክለኛና ብቃት ያለው የኮሙኒኬሽን ሰራዊት የሚባለው ሁሉንም በእኩል የሚያይና ሀሰተኞችን በትክክለኛ መረጃ የሚመክት ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በአራዳ ክፍለ ከተማ የኦሮሚያ ወጣት ማህበር ሰብሳቢ ታደሰ ኪላ መረጃዎች ወደ ህብረተሰቡ እንዲደርሱ ከማድረግ አንፃር በአፋን ኦሮሞ መረጃ ማስተላለፍ መጀመሩ ተደራሽነትን የማሳደግ ሚናው የጎላ ነው ብለው ሁላችንም ባሉን ስማርት ስልኮች አማካኝነት ትክክለኛውን መረጃ ከትክክለኛው አካል ወስደን ማጋራት አለብን ብለዋል፡፡

በመጨረሻም ከክፍለ ከተማ እስከ ብሎክ ድረስ የኮሙኒኬሽን ሰራዊት ግንባታ ላይ ውጤታማ ስራ በመስራት ላይ እንገኛለን ያሉት አቶ በላይነህ ሚዲያ ዘመናዊ የትግል ሜዳ እንደመሆኑ በሄዳችሁበት ሁሉ ሰላም፣ ፍቅርና አንድነትን ስበኩ ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡