Get Mystery Box with random crypto!

ቅሬታዎችን አስቀድሞ በመለየት በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ማገዝ፤ የአከላለል ጥያቄዎችን ለ | የጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ እውነተኛ ደጋፊዎች

ቅሬታዎችን አስቀድሞ በመለየት በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ማገዝ፤ የአከላለል ጥያቄዎችን ለሕገ ወጥ ተግባራት መጠቀሚያነት እንዳይውሉ ፍላጎት ያላቸው ተዋንያንን አስቀድሞ በመለየት ተገቢውን ርምጃ መውሰድ እንደሚገባ የደኅንነት ምክር ቤቱ አቅጣጫ ሰጥቷል።
በሶማሌ ክልል ከውጭና ከውስጥ የሚመነጩ የደኅንነት ሥጋቶችን ለመከላከል፣ ለመቋቋምና ለማስወገድ ወሳኝ ተግባራት መከናወናቸውን የደኅንነት ምክር ቤቱ በግምገማው አረጋግጧል። ሐምሌ 14 ቀን በአፍዴር ዞን በባሬና ጎት ጎት ወረዳዎች ሠርጎ ለመግባት የሞከረውን የአልሸባብ ኃይል ተከታትሎ ለመደምሰስ የክልሉ ልዩ ኃይል ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል። የክልሉ አመራር ሕዝቡን በማንቃት፣ በማሳተፍና በማደራጀት ጠላትን ለመደምሰስ ትምህርት ሰጪ እንቅስቃሴ አድርጓል። በሂደት የሀገር መከላከያ ሠራዊት የተሳተፈበት ኮማንድ ፖስት የተቋቋመ ሲሆን፣ በተካሄደ ኦፕሬሽን 813 አሸባሪዎች ተገድለው 79 ተማርከዋል። ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የጦር መሣሪያዎች፣ ተተኳሽ ጥይቶች፣ ፈንጂዎችና መገናኛ ሬዲዮኖች ተማርከዋል። ኮንትሮባንድን ለመቆጣጠር የሥጋት መሥመሮችን በመለየት ኬላዎች እየተጠናከሩ ቢሆንም አሁንም ሕገ ወጥ ተግባሩን በሚገባ ለመቆጣጠር አለመቻሉን፤ በጎሳዎች መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶችን ለመፍታት የጎሳ መሪዎችና አመራሩ በሚገባቸው ልክ አለመንቀሳቀሳቸውን፤ በጸጥታ ሥምሪት አፈጻጸም ላይ የሚታዩት የዲሲፕሊን ግድፈቶች መኖራቸውን፤ የአልሸባብን ሥጋትን በማስወገድ የውስጥ ደኅንነትን ለማረጋገጥ አሁንም የሚቀሩ ሥራዎች መኖራቸውን የደኅንነት ምክር ቤቱ በግምገማው አመላክቷል።
በአፋር ክልል የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን ለመቆጣጠር እየተሠራ መሆኑን የደኅንነት ምክር ቤቱ የገመገመ ሲሆን፣ በተለይም ዋናውን የኢትዮ-ጂቡቲ መሥመር ደኅንነት በማረጋገጥ በኩል ወሳኝ ሥራ መሠራቱን፤ ከአጎራባች ክልሎች ጋር በመነጋገር የጸጥታ ችግሮችን ለመፍታት እየተሞከረ መሆኑን ምክር ቤቱ በአዎንታ ተቀብሎታል። በአንጻሩ የጠላት እጅ የተጨመረበት የኮንትሮባንድ ንግድ አሠራሩን እየቀያየረ፣ አድማሱን እያሰፋ መምጣቱን፤ በጸጥታ ኃይሎች መካከል የቅንጅት ክፍተት መኖሩን፤ የጎሳ ግጭቶችን በኃላፊነት መንፈስ ለመፍታት የሚያስችል ሥራ በበቂ ሁኔታ አለመከናወኑን ምክር ቤቱ ገምግሟል። በመሆኑም በቀጣይ እነዚህ ወሳኝ ጉዳዮች ትኩረት አግኝተው፣ ተገቢ ውጤት ለማምጣት በሚያስችል ሁኔታ እንዲፈጸሙ አቅጣጫ አስቀምጧል።
ውድ ኢትዮጵያውያን፣
በትግራይ ክልል ያለው ሁኔታ በሰላማዊ መንገድ በድርድር እንዲፈታ መንግሥት አቅጣጫ መያዙና የተግባር እንቅስቃሴ ማድረጉ የአደባባይ እውነታ ነው። ድርድሩ ውጤት እስኪያመጣ ድረስ ለመቀጠል መንግሥት ቁርጠኛ መሆኑን ወዳጅም ጠላትም ተረድቶታል። በዚያ አካባቢ ያለውን የሥጋት ሁኔታም ከቀረበለት ሪፖርት በመነሣት የደኅንነት ምክር ቤቱ የገመገመ ሲሆን፤ ሁኔታዎች ከጸጥታ አካላት ዐቅም በታች መሆናቸውንና በተገቢው መንገድ ክትትል እየተደረገባቸው መሆኑን አረጋግጧል። ከግምገማው በመነሣት በአመራሩና በጸጥታ አካላት ሊከናወኑ የሚገባቸውን ተግባራት በመለየት አቅጣጫዎችን አስቀምጧል።
በአጠቃላይ የውስጥ ተጋላጭነትን በመቀነስ፣ ሀገራዊ ደኅንነትን ከማረጋገጥ አንጻር ከፍተኛ አዎንታዊ ለውጥ መምጣቱን፣ የፀጥታና ደኅንነት ጉዳይ ለመንግስት ብቻ የሚሰጥ አለመሆኑን በመገንዘብ ሕዝቡም የሥራው ባለቤት እየሆነ መምጣቱን ከግምገማው ለመገንዘብ ተችሏል። በሌላ በኩል ሥራዎች ገና አለመጠናቀቃቸውን፤ የጸጥታና ደኅንነት መዋቅሩ በሚጠበቀው መጠን አለመጥራቱን፤ የአመራሩንና የሕዝቡን የጸና ሥነ ልቡና የመገንባት ሥራ በተገቢው ልክ አለመሠራቱን፤ ጁንታው ከውስጥና ከውጭ ኃይሎች ጋር ሊያደርገው የሚፈልገውን ቅንጅት ለማምከን በልኩ አለመሠራቱን የደኅንነት ምክር ቤቱ ተመልክቷል። እነዚህ ጉዳዮች በተገቢው ትኩረትና ቁርጠኝነት ካልተሠሩ የተገኘው አንጻራዊ ሰላም ዘላቂ እንደማይሆን ገምግሟል። በመሆኑም የሚከተሉት ተግባራት በአመራር፣ በጸጥታ አካላትና በሕዝቡ ቁርጠኝነትና መሥዋዕትነት ሊተገበሩ እንደሚገባ አቅጣጫ አስቀምጧል።
1. አሸባሪና ሕገ ወጥ ታጣቂዎችን ሥጋት ከማይሆኑበት ደረጃ ማድረስ፣
2. ሕዝብን በማወያየት፣ የታጠቁ አካላትን በማግባባት፣ ወጣቶችን በሰላም ተግባራት ላይ በማሳተፍ፣ ዘላቂ ሰላም የሚያረጋግጡ
ሥራዎችን መሥራት፣
3. የፍትሕ አካላትን በማጥራትና በማጠናከር ለሀገራዊ ሰላምና ደኅንነት የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ ማድረግ፣
4. ሕዝቡን በሚያማርሩ የኢኮኖሚ አሻጥር፣ የሙስና፣ የኮንትሮባንድ፣ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ወዘተ ላይ የማያዳግም ርምጃ
በመውሰድ ሕዝቡ እፎይ እንዲል ማድረግ፣
5. በየደረጃው ያለውን አመራር በማጥራትና ተጠያቂነትን በማስፈን፤ በየደረጃው ብቁ፣ ንቁና ወትሮ ዝግጁ የሆነ አመራር መፍጠር፣
6. ሕዝባዊና የሃይማኖት በዓላትን፣ የብሔርና የአስተዳደር እርከን ጥያቄዎችን፣ ጠላት የዓላማው ማስፈጸሚያና የሕዝቡን ሰላም
ማወኪያ እንዳያደርጋቸው፣ ከሚመለከታቸው ጋር በመቀናጀት መሥራት፣
7. በአፋርና በዒሳ መካከል፣ በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን የሚታዩ የጸጥታ ሥጋቶችን በዘላቂነት ለመፍታት ተገቢውን
የፖለቲካና የጸጥታ ሥራ መሥራት፣
8. አልሸባብ ከውጭና ከውስጥ ኃይሎች ጋር ተቀናጅቶ የሥጋት መጠኑን ለመጨመር እንዳይችል፣ የተቀናጀ የጸጥታ ኃይሎችና
የሕዝብ ሥምሪት ማካሄድና በቀጣናው ትርጉም ያለው ኃይል እንዳይሆን ማድረግ ቀጣይ ተግባሮቻችን ናቸው።
አመራሩ፣ የጸጥታ መዋቅሩና ሕዝቡ ተግባብቶና ተቀናጅቶ ሲሠራ ምን ዓይነት አመርቂ ውጤት እንደሚመዘገብ ካለፉት ሥራዎቻችን በሚገባ ተምረናል። በቀጣይም ይሄንኑ አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል። እያንዳንዱን ተግባር ቆጥሮና ኃላፊነት ወስዶ ማከናወን፣ በየጊዜው መገምገም፣ የሠሩትን ማበረታታትና ኃላፊነታቸውን የማይወጡትንም መቅጣት ይገባል። በእያንዳንዱ አካባቢ የሚከናወነው ጸጥታንና ደኅንነትን የማረጋገጥ ተግባር የመላዋ ኢትዮጵያ ሰላም የሚያጸና መሆኑን ማመን ያስፈልጋል። አጠቃላዩ ነገር የቅንጣቶቹ ድምር ውጤት፣ አንዳንዴም ከቅንጣቶቹ ድምር በላይ ነው። አጠቃላዩን የጸጥታና የደኅንነት ሁኔታ የተሻለ ለማድረግ እያንዳንዳችን በተሠማራንበት መስክ የምናከናውን ቅንጣት ተግባር በጥራትና በብቃት መወጣት ይገባናል።
ሕዝባችን ሰላሙና ደኅንነቱ ተረጋግጦለት ኢትዮጵያን ለማበልጸግ በሚደረገው ርብርብ ንቁ ተሳታፊ እንደሚሆን በየደረጃው በተካሄዱ ውይይቶች በአንድ ቃል ተናግሯል። በየጊዜው የምናደርጋቸው የግምገማ ውይይቶች፣ አዳዲስ ምክንያቶችን የምንሰማባቸው ሳይሆኑ፣ የችግሮችን መቀነስና የሰላምና ደኅንነትን መስፈን የሚያረጋግጡ መሆን አለባቸው። ይህ ደግሞ የሚሳካው ዕቅድን በሚገባ በመገንዘብ፣ የሚያስፈልገውን ሥምሪት በማካሄድና እስከ መጨረሻው ድረስ ለውጤቱ ብቻ በመድከም ነው። ስለሆነም በየደረጃው ያሉ አመራሮች፣ የጸጥታ ኃይሉና ሕዝቡ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ፣ እንደ አንድ ልብ መካሪ ሆኖ የኢትዮጵያን ጸጥታና ደኅንነት ለማረጋገጥ እና ብልጽግናዋን እውን ለማድረግ ቁርጠኞች እንድንሆን ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤቱ ጥሪ ያቀርባል።
//
የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት
ነሐሴ 2፣ 2014 ዓ.ም
አዲስ አበባ

የቴሌግራም ቻናል https://t.me/abdisira
የፌስ ቡክ ግሩኘ https://facebook.com/groups/1214264802267291/